Sat02172018

Last updateTue, 24 May 2016 11am

Back You are here: Home የምርጫ ዜናዎች የ2007 የኢትዮጵያ ምርጫ ለለውጥና ለዴሞክራሲ እድገት

የ2007 የኢትዮጵያ ምርጫ ለለውጥና ለዴሞክራሲ እድገት

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በመጪው ግንቦት 16 አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል። ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ የካቲት 7ቀን ተጀምሮ ግንቦት 13 ቀን ይጠናቀቅና አጠቃላይ የምርጫ ውጤትም ሰኔ 15 ቀን ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ቀደምት የኢትዮጵያ ምርጫዎች ዳሰሳ
ከወታደራዊው የደርግ መንግስት መውደቅ በሁዋላ የ1987ቱ ህገ-መንግስት በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ለአራት ተከታታይ ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህ አዴግ) አሸናፊነቱን ሲያበስር ቆይቷል።
ሶስተኛውና በ1997 ዓ .ም የተካሄደው አገራዊ ምርጫ ምንም እንኳ ውጤቱን ተከትሎ ከፍተኛ ረብሻና ህዝባዊ አመጽ የተስተናገደበት ቢሆንም ከጅምሩ የነበረው ሂደት ግን ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል። ይሁን እንጂ በዚህ ምርጫ፤ ከምርጫው እለት ማግስት ጀምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች እያሸነፉ መሆኑ መሰማት ጀመረ። ከዚህም ባሻገር አጠቃላይ የምርጫ ውጤት መዘግየት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በህዝቡ ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ። በሁዋላም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከ 547 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ገዢው ፓርቲ የ372 ፓርላማ መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ ተቃዋሚዎች ደግሞ 172 ወንበሮችን ማሸነፋቸውን ሲገልጽ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጤቱን ባለመቀበል ምርጫው ተጭበርብሯ ሲሉ ገለጹ። ይህም ህዝቡ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን እንዲገልጽ ምክኒያት ሆነ። በዚህም ሳቢያ ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ በቀጥታ በመተኮስ ለብዙዎች ህይወት ማለፍ ሰበብ ሆኗል።
በመቀጠልም መንግስትን በሀይል ለመጣል መሞከር በሚል ወንጀል 131 የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላቱ ወደ ወህኒ ተወረወሩ። ከዚህም መካከል 21 የግል ጋዜጠኞች ናቸው።
በመጨረሻም ገዢው ፓርቲ የመንግስት ስልጣንን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ በቁጥጥሩ ስር እንዲያውል አድርጎታል። ከዚያ ቀጥሎ በተካሄደው አራተኛው የ2002 ዓ.ም ምርጫ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲና ከሌላ አንድ የግል ተወዳዳሪ በስተቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ (99.6 በመቶ ) የፓርላማ ወንበር ገዢው ፓርቲ ብቻውን ሲቆጣጠረው ያን ያህል አስገራሚ ያልሆነው በዚሁ ምክኒያት ነው።

የ 2007 አገራዊ ምርጫ
የዚህ አመቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው። ሀገሪቱን ለሀያ አንድ አመታት የመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በመስከረም ወር 2005 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጡት ሀይለማሪያም ደሳለኝ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለሁለት አመታት ያህል አገልግለዋል። በሁለት መቶ አመታትየኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ ከትግራይና ከአማራ ብሄረሰብ ዉጪ የሆነ መሪ ወደ ስልጣን ሲመጣ ሀይለማሪያም የመጀመሪያው ናቸው።
በሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ 23ቱ በብሄራዊ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ ወገንተኛና በሚንቀሳቀሱበት ክልልም የፓርቲው ፕሮግራም አስፈጻሚዎች ናቸው። በተቃዋሚ ጎራ ከተሰለፉት መካከልም አምስት ያህል ጠንካራ ተቀናቃኝና ሰፊ የህዝብ ይሁንታን ያገኙ ሲሆን እነሱም፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የፓርቲዎች ጥምር የሆነው መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው።

የቀጣዩ ምርጫ አጠቃላይ ሁኔታ ዳሰሳ
ይህ ምርጫ የሚካሄደው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ባስመዘገበችበት በዚህ ወቅት ነው። ሀገሪቱ 10 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ትልቁ ውጤት ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ በአለም አቀፍ ህብረተሰብ ዘንድ መልካም ስም የላትም። በተለይም የመገናኛ ብዙሀን ነጻነትን በተመለከተ አስከፊ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሳለች። ኢትዮጵያ ከጎረቤትዋ ኤርትራ በመቀጠል ጋዜጠኞችን ወደ ወህኒ በመወርወር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሀን የሚባሉት የቴሌኮሚኒኬሽንን ጨምሮ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ከመሆናቸውም ባሻገር በግሉ ዘርፍ ያለውም ቢሆን ጫና በሚያሳድሩ አፋኝ ህጎች ስር የወደቀና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። ለነጻ ሚዲያው ዕድገት ማነቆ የሆኑት ሌሎች ምክኒያቶች ደግሞ በግል ሚዲያው ላይና የሲቪል ማህበራት ላይ የሚጫነው ከፍተኛ የገንዘብ ጫና፣ ዝቅተኛ የጋዜጦች ህትመትና ስርጭት እንዲሁም የተሟላ የመገናኛ ዘዴዎች መሰረተ ልማት እጥረት ናቸው።
አርቲክል አስራ ዘጠኝ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆች አመት (2014) ላይ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በቃኘበት ሪፖርቱ እንደ ገለጸው ምንም እንኳ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2009 የተሰጣትን አስተያየቶችና ግምገማ በወቅቱ የተቀበለቻቸው ቢሆንም በተግባር ላይ እንዳላዋለቻቸው ጠቅሷል። በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የመረጃ ነጻነት ከመሻሻል ይልቅ ከዕለት ወደ ዕለት እየደበዘዘ መምጣቱን አስታውሷል።
በ 2007 ምርጫ መንግስት የተሰጡትን አስተያየቶች በመቀበል ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ ለማዋልና በሀገሪቱ ህገ መንግስት የተጠቀሱትን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብቶች ለማክበር እንዲሁም ከምርጫው ቀደም ብሎ ፖለቲካዊ ውይይቶችና ክርክሮችን ለማበረታታት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በአሁን ሰአት እየሆነ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።

የጸረ ሽብር ህጉን በተመለከተ
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ የዞን ዘጠኝ አባላት የሆኑ ስድሰት ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው በዚሁ የጸረ ሽብር ህግ ተከሰዋል። በወቅቱም አርቲክል አስራ ዘጠኝ ጉዳዩ እንደሚያሳስበውና ይህ ህግ ከዚህ ቀደምም 22 ያህል ጋዜጠኞችን ለእስር የዳረገ እንዲሁም የጋዜጠኞችን አለም አቀፍ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጻረር መሆኑን ገልጾዋል።
ከዚህም ባሻገር የጸረ ሽብር ህጉ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ኮሚሽን፣ በአፍሪካ የስብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በሰብአዊ መብት ኮሚቴና በተባበሩት መንግስታት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ልዩ ጥበቃና ተከራካሪ ቡድን ከፍተኛ ተቃዉሞ ቀርቦበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ እንዳለበት በመርህ ደረጃ የሚያምን ቢሆንም በድርጊት ግን ፍጹም ተቃራኒ ነው።

የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጾችና የጋዜጠኞች ክስ
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በ2004 ዓ.ም ነሀሴ ወር ማገባደጃ ላይ ይፋ ከመሆኑ በፊት ለሁለት ወራት ያህል ከሚዲያ መጥፋታቸው ጉዳዩ በሚስጥር በመያዙ በህዝብ ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ይህንኑ ጉዳይ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ወደ ህትመት ያመጣው። ይሁን እንጂ ተመስገንና የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ማስተዋል ብርሀኑ በዚሁ ጉዳይ ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበው ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት በሚል ወንጀል ተከሰዋል። በተመሳሳይ አንቀጽ ሌላ ክስ ከሁለት አመት ክርክር በሁዋላ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ወር ላይ የሶስት አመት ፍርደኛ ሆኖ ወደ ወህኒ ሲወርድ አሳታሚው ደግሞ የአስር ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎበታል።
በእንደዚህ አይነት ተመሳሳይ ህጎች ብዙ ጋዜጠኞች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ሆነዋል። መንግስት እንደነዚህ አይነት ህጎችን ከሱ ሀሳብ በተቃራኒ የሚቆሙትን ለማጥቃት በይፋ በመጠቀም ላይ ይገኛል።
በመስከረም ወር 2007 ዓ .ም እንዳልካቸው ተስፋዬ (አዲስ ጉዳይ መጽሄት)፣ ግዛው ታዬ (ሎሚ መጽሄት)፣ እንዲሁም ፋጡማ ኑርያ (ፋክት መጽሄት) የሀሰት መረጃ በማሰራጨት፣ አመጽ በመቀስቀስና መንግስትን በሀይል ለመጣል መሞከር በሚል ተከሰው የሶስት አመት እስራት በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል።

ቀጣዩ ምርጫና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ጠቀሜታ
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሙሉ በሙሉ ማክበር ለቀጣዩ ምርጫ ወሳኝና ዋነኛ ጉዳይ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርአት ዜጎች ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ተመራጭ በመስጠት የራሳቸውን መንግስት በነጻነት ይመርጣሉ። ይንንም ለማድረግ እንዲችሉ ስለሚመርጧቸው እጩ ተወዳዳሪዎች ማንነትና ስላቀዷቸው ፕሮግራሞች ሙሉ መረጃ ሊቀርብላቸው ይገባል። ይህንንም ለማስፈጸም ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ መኖሩ አስፈላጊ ነው። ሁሉም እጩ ተወዳዳሪዎችም እኩል የሆነ የመገናኛ ብዙሀን ሽፋን ሊሰጣቸው ይገባል። በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀንም ቢሆኑ መረጃን በነጻነት ማሰራጨት ይኖርባቸዋል። ያለ ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ የመንግስትን ፕሮግራሞች ለማስፈጸም አይቻልም። መረጃን በነጻነት ለማግኘት ተግባራዊ ህጎች ሊኖሩ ይገባል። በመሆኑም የመረጃን ነጻ ፍሰት የሚገድቡ ማናቸውም ህጎች ቢሆኑ ተግባራዊ መሆን የለባቸውም።

ሊሻሻሉ ስለሚገባቸው ህጎች

በኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ የዋሉት የተለያዩ አፋኝ ህጎች ማሻሻያ ካልተደረገባቸው በስተቀር የሀገሪቱን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማሻሻል አይቻልም። እነዚህ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጎች፤

1. የጸረ ሽብርተኝነት ህግ
2. የወንጀለኛ መቅጫ ህግ
3. የመገናኛ ብዙሀን አዋጅ
4. የስም ማጥፋትን የሚመለከቱ አንቀጾች
5. የመንግስት ሹማምንትን ስለመተቸት የሚጠቀሱ አንቀጾች
6. በሀገር ደህንነት ሳቢያ የተጣሉ ክልከላዎችን አለም አቀፍ ደረጃን እንዲጠብቁ ማድርግ ናቸው።

ቀጣዩ ምርጫና የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለመቀየር ያለው ድርሻ
በዚህ ምርጫ የሚሳተፉ አካላት ሁሉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ዕድሉን መጠቀም አለባቸው። ሀገሪቷ አሁን ያለችበት የመረጃ ነጻነትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በአግባቡ ጥናት ሊደረግበት ይገባል። ከምርጫው በሁዋላ ወደ መንግስት ስልጣን የሚመጣው ሀይል በዚህ ረገድ ሁነኛ መሻሻሎችን ለማምጣት ተግባራዊ የሚሆን ፕሮግራም ሊኖረው ይገባል። ይህም የመንግስት አስተዳደር ባህልን በመቀየር መደገፍ አለበት። መንግስት ከድብቅነትና ከሀይለኝነት ይልቅ ወደ ግልጽነትና ወደ ተጠያቂነት መሸጋገር ይኖርበታል።