Tue02202018

Last updateTue, 24 May 2016 11am

Back You are here: Home Features የኢትዮጵያ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ፡ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የሚደረግ ገደብ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ፡ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የሚደረግ ገደብ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡

 


ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ አምስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ የምታካሄድ ሲሆን ይኼም ለረዥም ጊዜ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በይፋ የሚጠናቀቅ ሲሆን የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ግልጽ ይሆናል፡፡


ባለፈው አንድ ዓመት አርቲክል 19 ምርጫውን የተመለከቱ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው ሃሳብን የመግለጽ እና የመደራጀት ነጻነት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል፡፡ ይኽም ምርጫው ነጻ እና ፍተሃዊ የመሆን እድሉን አጨልሞታል፡፡


የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ግርሻ


በሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የደርግን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ በ1983 ዓ.ም. ስልጣን ይዟል፡፡ ፓርቲው ቀደም ሲል በ1987፣ 1992፣ 1997 እና 2002ዓ.ም. የተካሄዱ ምርጫዎች አሸናፊ መሆኑን አውጇል፡፡


ከፍተኛ ውድድር የነበረበት እና ገዢው ኢህአዴግ ስልጣሉን ሊያጣ የደረሰበት ወቅት በመሆኑ ምክንያት በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ እና በዚህም ምክንያት የተፈጠረው ብጥብጥ ለሃገሪቱ እንደ አንድ ዋና ምዕራፍ የሚጠቀስ ነው፡፡ የምርጫ ውጤቱ ሲታይ ተቀዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠበቀ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘት እና ከፍተኛ የፓርላማውን ወንበሮች ማሸነፍ ችለው ነበር፡፡ የመርጫ ውጤቱ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ሲዘገይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ተቃውሞው ወደ ብጥብጥ ተቀይሯል፡፡ በመጨረሻም ይፋዊ የምርጫ ውጤቱ ሲወጣ ( 372 መቀመጫ ለኢህአዴግ፣ 172 መቀመጫ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች) የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ምርጫው “መጭበርበሩን” ገለጹ፡፡ በዚህ ምክንያት በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ፖሊስ ወደ ህዝቡ ቀጥታ በመተኮስ በርካታ ሰልፈኞችን ገድሏል፡፡


21 ጋዜጠኞችን ጨምሮ 131 ፖለቲከኞች የታገቱ ሲሆን በኋላም መንግስትን በሃይል ለመገልበጥ በመሞከር የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ኢህአዴግ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ያለማንም የጎላ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳድሮ 99.6 በመቶ ማሸነፉን ብዙም ገራሚ ጉዳይ የማያደርገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ፓርቲው ሁለት መቀመጫዎችን ብቻ ሲሆን የተሸነፈው ይኼውም አንዱ በተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ አንዱ ደግሞ በግል ተወዳዳሪ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ለ2007 ዓ.ም. ምርጫ ምን ማድረግ እንዳለበት ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሂደት ትምህርት የቀሰመ ይመስላል ይሄውም ምርጫው ከመካሂዱ ወራት ቀደም ብሎ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንን እና ተሟጋቾችን ለማጥፋት ጥረት አድርጓል፡፡” ብለዋል የአርቲክል 19 ምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሄነሪ ማይና፡፡


ሚያዚያ 12 እና 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ዓ.ም. ሰባት የዞን 9 ጦማሪያን አባላት - ሶሊያና ሽመልስ (በሌለችበት የተከሰሰች)፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ዘላለም ክብረት፣ እና አቤል ዋቤላ -የታሰሩ ሲሆን በኋላም ከሶስት ጋዜጠኞች - ኤዶም ካሳዬ፣ ተስፋለም ወልደየስ፣ እና አስማማው ወልደጊዮርጊስ- ጋራ አንድ ላይ በጸረ-ሽብር አዋጁ (652/2000) ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡


መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዳልካቸው ተስፋዬ (አዲስ ጉዳይ መጽሔት)፣ ግዛው ታዬ (የሎሚ መጽሔት አሳታሚ) እና ፋጡማ ኑርዬ (ፋክት መጽሔት) በሌሉበት ከሶስት ዓመት የበለጠ እስር ተበይኖባቸዋል፡፡ክሶቹ ብጥብጥ ለመቀስቀስ፣ ያልተጣሩ አሉባልታዎችን በማተም እና በማሰራጨት እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ የሃገሪቱን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለማፈራረስ በማሴር የሚሉ ናቸው፡፡ ሦስቱም ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት በስደት ላይ የሚገኙ ስሆን መጽሔቶቹም መታተም አቁመዋል፡፡ በእነዚህ ክሶች እና በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ሌሎች መጠነ-ሰፊ ማስፈራሪያዎች ምክንያት ሊመጣ የሚችል እስርን በመፍራት ቢያንስ 30 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ባለፉት 18 ወራት ሃገሪቱን ለቀው ተሰደዋል፡፡ ሌላው የፈጠረው አሉታዊ ተፅእኖ ደግሞ በምርጫው ዙሪያ የሰላ ትችት እና ትንታኔ ሊያቀርቡ የሚችሉ መገናኛ ብዙሃን አንደበትን እንዲሸበብ ማድረጉ ነው፡፡


መንግስት የመገገናኛ ብዙሃን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጣሪ እንደሆነ ነው፤ ይኼም ብቸኛው ብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጣቢያ የሆነውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)ይጨምራል፡፡ የክልል መንግስታትም የክልል መገናኛ ብዙሃንን የተቆጣጠሩ ሲሆን ይኼም የድሬ ዳዋ ቴሌቪዥን እና የኦሮሚያ ቴሌቪዥንን ይጨምራል፡፡ አብዛኛው የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው፤ ካልሆነም ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር የሚጣጣም ፍላጎት ባላቸው ወይንም የተለየ ቅርርብ ባላቸው አካላት የተያዙ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ ሶስት ብቻ ዕለታዊ ጋዜጦች ነው የሚገኙት፤ በመንግስት የሚተዳደሩት አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያን ሄራልድ እና በግል የተያዘው ዴይሊ ሞኒተር፡፡ በመንግስት የሚተዳደሩ ሳምንታዊ ጋዜጦች አል-አለም (በአረበኛ የሚታተም)፣ እና በሪሳ (በኦሮምኛ የሚታተም) ሲሆኑ የስርጭት መጠናቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአጠቃላ የሃገሪቱ ህዝብ ብዛት አንጻር ሲነጻጸር በቀን ያለው ህትመት በአጠቃላይ ከ100 ሺህ አይበልጥም፤ 87.4 ሚሊዮን ህዝብ ለሚኖርባት ሀገር ይህ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የግል ጋዜጦች እና መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እንዲዘጉ ተደርጓል፤ አዲስ ፕሬስ፣ አዲስ ወሬ፣ አውራምባ ታይምስ፣ ቢዝነስ ኮንስትራክሽን፣ ዳጉ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ 7 ደይስ አፕዴት፣ ጎግል፣ ሰነድ፣ ሶውተል-ኢስላም፣ ጥበብ-ኢትዮጵያ፣ ኢትዮ-ቻናል፣ ቆንጆ፣ ዕንቁ፣ ጃኖ፣ አዲስ ጉዳይ፣ አስማት፣ ፋክት እና ሚኒሊክ ይገኙበታል፡፡


“በዚህ ወቅት ያለው ሁኔታ ያስፈራል፡፡ አብዛኛው የግል ህትመት ውጤቶች ተዘግተዋል፤ በርካታ ጋዜጠኞችም ሃገሪቷን ለቀው ተሰደዋል ይሄውም በስራቸው ምክንያት በተከታታይ እየደረሰባቸው ባለው ማስፈራሪያ እና አካላዊ ጥቃት ነው፤ የተቀሩት ደግሞ በእስር ላይ ነው የሚገኙት፡፡” ብሏል አስራት አብርሃም በወቅቱ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ቃል-አቀባይ ጥር 2007 ዓ.ም. በሰጠው ቃለ-መጠይቅ፡፡


ይህን ንግግር የሰማያዊ ፓርቲ ቃል-አቀባይ በሆነው ዮናታን ተስፋየም የተደገፈ ነው “ሆነ ተብሎ የተደረገ ነገር ነው፡፡ ከምርጫ 1997 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ነጻ መገናኛ ብዙሃን እንዲኖሩ አይፈልግም፤ ያኔ በአንጻራዊ ሁኔታ መገናኛ ብዙሃኑ ነጻ ነበሩ፤ ህዝቡም የተሸለ መረጃ ነበረው፡፡”


የአርቲክ 19ኙ ማይና በበኩሉ “ሁሉንም ድምጾች ሊያስተጋባ የሚችለው ነጻ እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ አለመኖር ለዚህ ምርጫ የሚደረገውን የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳ ጎድቶታል፡፡መራጩ ህብረተሰብ ለምርጫ የቀረቡት እነማን ስለመሆነቸው፣ እንዲሁም ስለፖሊሲዎቻቸው በተለይ ደግሞ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ የተሟላ መረጃ አለው ብለን አናምንም፡፡” ብሏል፡፡


መንግስት የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብትን ገድቧል


በበርካታ አጋጣሚዎች በሰማያዊ ፓርቲ፣ በዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር እና በአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የተዘጋጁ የተቃውሞ ሰልፎችን ፖሊስ በሃይል በትኗል፤ ይህም በአዲስ አበባ እና የተለያዩ የክልል ከተሞች የተደረጉ ተቃውሞ ሰልፎችን ይጨምራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተደጋጋሚ እነዚህ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንዳያካሂዱ ፍቃድ ከልክሏል፡፡ ሆኖም የኢህአዴግ እንቅስቃሴዎች ያለምንም እንቅፋት ሲተገበሩ ተስተውሏል፡፡


ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የአንድነት ፓርቲ ያካሄደው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ በሃይል ተትኗል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን ለመዘገብ የተገኙ በርካታ ጋዜጠኞች እና የፓርቲው አመራሮች ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአካላዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ የተካተቱበት የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር የተጠራውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የፌዴራል ፖሊስ በሃይል እንዲበተን አድርጎታል፡፡ ፖሊስ በወቅቱ የዘጠኙን ፓርቲዎች አመራር አባላት በዘፈቀደ ያሰረ ሲሆን ከእነሱም ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት ይገኙበታል፡፡


የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ለማግኘት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፈተና


መንግስት አብዛኛውን የግል መገናኛ ብዙሃን ስለዘጋው እና የቀሩትም የመገናኛ ብዙሃን በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ስለሆነ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንቦት 16 ቀን ለሚደረገው ምርጫ ዝግጅት መልዕክታቸውን ለመራጬ ህዝብ ለማድረስ ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ ተገደዋል፡፡


“ፓርቲያችን የዲያስፖራ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም መረጃ ለማሰራጨት እየሞከረ ይገኛል፤ የሰማያዊ ፓርቲን ጋዜጣም በኢንተርኔት እያተመን እንገኛለን” ብሏል ዮናታን፡፡ እንደ አስራት መረጃ ደግሞ ፓርቲው የራሱ የህትመት ውጤት ያለው ሲሆን ሳምንታዊውን ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እያተመ ይገኛል፡፡ ጋዜጣዋ በቅርቡ ወደስርጭት የተመለሰች ናት፤ በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. በመንግስት ስር ሚተዳደረው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋዜጣዋን ማተም አቁሞ ነበር፡፡ ፓርቲው የሚሊዮኖች ድምጽ የሚል ሌላ ጋዜጣም በኢንተርኔት እና በወረቀት ማሳተም ጀምሮ ነበር፡፡ “ማሕበራዊ ድረ ገጽን ጨምሮ የተገኘውን አማራጭ ሁሉ በመጠቀም መልዕክታችንን ለማሰራጨት እየሞከርን ነው፡፡” ብሏል አስራት የካቲት 2007 ዓ.ም. በተደረገለት ቃለ-መጠይቅ፡፡ አንድነት የራሱን ጋዜጣ የሚያትመው ራሱ ሲሆን የህትመት ብዛቱ ግን በሳምንት ከ2000 ኮፒ ያነሰ ነው፡፡


የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠቀሟቸው ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ (ቪኦኤ) እና የጀርመን ራዲዮን (ዶቼ ዋለ) የሚያካትት ሲሆን ሁለቱም መገናኛ ብዙሃን በአማርኛ አጭር ሞገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰራጨሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱንም ጣቢያዎች የአየር ሞገድ ለመገደብ ሞክሯል የሚል ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡ ከአምስተርዳም፣ ሎንዶን እና ዋሽንግቶን ዲሲ በቀን ለ24 ሰዓት በአማርኛ የሚሰራጨው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም (ኢሳት) ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በጎ ሽፋን ይሰጣል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2002 ዓ.ም. አየር ላይ የበቃው ጣቢያ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ መንግስት የአየር ሞገዱን ለማገድ ጥረት እየተደረገበት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ኢሳትን በግንቦት ሰባት የሚመራ ነው በማለት ይከሳል፤ ግንቦት ሰባት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት ነው፡፡


በህዝብ መገናኛ-ብዙሃን ከተመደበው የአየር ሰዓት እና ቦታ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል


ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራ ምርጫ ቦርድ ለግንቦት 16 ቀኑ ምርጫ የሚወዳደሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ስርጭት አየር ሰዓት እና የጋዜጦች የማስታወቂያ ቦታ አጠቃቀም ክፍፍል አውጥቷል፡፡ አብዛኛው የአየር ሰዓት እና ቦታ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ተወስዷል፡፡


የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን በሚከተለው መስፈርት ነው የተከፋፈለው፡


• አርባ በመቶው የተመደበው እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገሪቱ ፓርላማ እና የክልል ምክር-ቤቶች ባላቸው ወንበር ቁጥር ብዛት
• አርባ በመቶው ፓርቲዎች ባላቸው ተወዳዳሪ እጩዎች ብዛት
• አስር በመቶው ፓርቲዎች ባላቸው የሴት እጩዎች ብዛት
• አስር በመቶው ደግሞ ለሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የተከፋፈለ ነው፡፡


ለብሄራዊ ምርጫ የቀረቡ እጩዎች እና ፓርቲዎች በብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት እና ቦታ የተመደበላቸው ሲሆን በክልል ደረጃ የሚወዳደሩ እጩዎች ደግሞ በየክልሎቻቸው የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ላይ የአየር ሰዓት እና ቦታ ተከፋፍለዋል፡፡


በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ከተመደበው የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ ቦታ 55 በመቶው በፓርላማ እና የክልል ምክርቤቶች ውክልና ላላቸው ፓርቲዎች ነው የተመደበው፣ 20 በመቶው ደግሞ ለሁሉም እጩዎች የተመደበ ሲሆን 25 በመቶውን ሁሉም ፓርቲዎች በእኩል እንዲከፋፈሉት የተመደበ ነው፡፡ “በዚህ አመት ያለው የአመዳደብ ሁኔታ አዲስ መስፈርት ፈጥሯል፤ ይኼውም የሴቶችን ውክልና የተመለከተ ነው፡፡ ሆኖም የክፍፍሉ መስፈርት አሁንም ፍትሃዊ አይደለም፤ በተለይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ፍትሃዊ አይደለም፡፡” ብሏል ማይና


ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በህዝብ ተዎካዮች ምክር-ቤት እና የክልል ምክር-ቤቶች አብላጫ ወንበር አለው፤ ይኽም ማለት በመጨረሻው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ ሁሉንም የተመደበ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ ቦታ ይጠቀማል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በርካታ ተወዳዳሪ እጩዎችን ለማቅረብ የሚያስችል የገንዘብ እና የአቅም ውሱንነት ስላለባቸው ገዢው ፓርቲ በእጩዎች ብዛት ከተመደበው አርባ በመቶ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ ቦታ አብዛኛውን የመውሰድ እድሉም የሰፋ ነው፡፡


አርቲክል 19 በዚህ ፍትሃዊ ባልሆነ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ክፍፍል ላይ ቅሬታ አለው፡፡ በምርጫ ወቅት ለግልጽ ክርክር እንዲሁም እጩዎች እና ፓርቲዎች ለዜጎች ፖሊሲዎቻቸውን በተመለከተ ለህዝብ መረጃ ለማደረስ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን በዋጋ ሊተመን የማይችል ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህም መራጮች በመረጃ የተመሰረተ ድምጽ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል፡፡ የዚህ የመጨረሻ ነጥብ ጠቀሜታ በቸልታ ሊታለፍ የሚችል አይደለም፤ ምክንያቱም የመራጮች በመረጃ የተመሰረተ የምርጫ ውሳኔ አቅም ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን እኩል እንዲጠቀሙ ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ያለው፡፡


ኢቢሲ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማስታወቂዎች ላይ ቅድመ ምርመራ ያደርጋል


ለምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ያዘጋጇቸውን ማስታወቂያዎች ያለአግባብ መንግስትን የሚተቹ ናቸው በማለት ለማስተላለፍ ባለመፍቀዱ ምክንያት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢቢሲን ቅድመ ምርመራ ያደርግብናል በማለት ወቅሰዋል፡፡ ይህም ማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በተመደበውን የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ክፍፍል መሰረት የደረሳቸውን የአየር ጊዜ መጠቀም እንዳይችሉ ሆነዋል፡፡


በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ (መድረክ) የተዘጋጀ አንድ የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያ የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም በኢቢሲ እንዳይተላለፍ የታገደ ሲሆን ምክንያቱም የመንግስትን ስርዓት እና መንግስታዊ ተቋማትን ይተቻል የሚል ነው፡፡ “ሊሰራጭ የቀረበው መልዕክት በሃገሪቱ በዓሁኑ ወቅት ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ይክዳል እንዲሁም ለመንግስት ተቋማት እውቅና አይሰጥም፡፡ ይህም ዜጎች በመንግስት ላይ እምነት እንዳሳደሩ ሰለሚያደርግ ልናስተላልፈው አንችልም፡፡” ይላል ከኢቢሲ ለመድረክ የፓርቲዎች ጥምረት የተላከው ደብዳቤ፡፡
“ኢቢሲ የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎችን ሊያስተላልፍ የሚችለው ከድርጅቱ የኤድቶሪያል ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ህጉ ወይንም ሌላ አሳማኝ ምክንያት ድርጅቱ የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎችን ያለማሰተላለፍ መብት አለው፡፡” ይላል ለመድረክ የተላከው ደብዳቤ፡፡


“ይህ ሙሉ በሙሉ የቅድመ ምርመራ ስራ ነው፤ ህገ መንግስታዊ መብታችንንም ይጥሳል፡፡” ብሏል የሰማያዊ ፓርቲ ቃል-አቀባይ ዮናታን ተስፋዬ ሃገር ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፡፡ “በምረጡኝ ቅስቀሳችን ወቅት የሃገሪቱን ህግ የሚጥስ ነገር ከፈጸምን ፍርድ ቤት ሊያቀርቡን ይችላሉ፡፡ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ከመራጩ ህዝብ ጋር እንዳንገናኝ ሊያግዱን አይችሉም፡፡”


የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በተደጋጋሚ በኢቢሲ፣ ዛሚ ራዲዮ ኤፍ ኤም 90.7 እና ፋና ብሮድጋስቲንግ ኮርፖሬት የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻዎቹ ላይ ቅድመ-ምርመራ በተደጋጋሚ እንደሚካሄድበት ገልጾ ፓርቲው ሚያዚያ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በመገናኛ ብዙሃን የተመደበለትን የአየር ሠዓት ላለመጠቀም ወስኗል፡፡ ኢቢሲ እና ዛሚ ሬድዮ እያንድ አንዳቸው አንድ አንድ ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ ሲሆን ፋና ደግሞ ሁለት ማስታወቂያዎችን እንዳይተላለፉ ማገዱን ፓርቲው ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ “መገናኛ ብዙሃኑ የሚያቀሩቧቸው ምክንያቶች እንደሚያሳዩት የመልዕክቶቹ ይዘት የመንግስት ተቋማትን እምነት የማሳጣት እና ተዓማኒነታቸው ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ አሉታዊ ጉዳዮች ይካተቱበታል” ብለዋል፡፡


እንዳይተላለፉ የታገዱት ፕሮግራሞች በዋናነት የተለያዩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አሰራሮችን በመተቸት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዛሚ ራዲዮ ለማስተላለፍ የከለከለው አንዱ ፕሮግራም ህገ-መንግስቱን ለመቀየር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እና ሃገሪቱ ይሄንን ህግ ማሻሻል እንደሚገባት የቀረበ ውይይትን ነው፡፡ ሌላው የኢዴፓ ፕሮግራም የሃገሪቱ ብሄራዊ ጦር የተሰማራበት ኢኮናሚያዊ መስክ ገደብ ሊበጅለት ይገባል የሚል እና በማጠቃሊያውም ኢዴፓ ስልጣን ከያዘ ኢህአዴግን በመቃዎማቸው ለእስር የተዳረጉ የፖለቲከኛ እስረኞችን ምህረት እንደሚያደርግላቸው የሚጠቅስ ነው፡፡
በምርጫ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ከገዢው ፓርቲ ፖሊሲዎች ጋር እያገናዘቡ እና እያነጻጸሩ ማቅረብ የተለመደ ሲሆን ይሄም የመራጩን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት፣ በተግባር ላይ የዋሉ ህጎችን እና ተቋማትን መተቸት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አንዱ አካል ስለሆነ ቅድመ-ምርመራ ሊያደርግበት አይገባም፡፡


የቅድመ-ምርመራ ጉዳይ እና ፍትሃዊ ያልሆነ የአየር ሠዓት ክፍፍል በቴሌቪዥን በተሰራጨ ክርክር ላይም ተስተውሏል፡፡ ኢቢሲ በምርጫ ዙሪያ 9 ክርክሮችን ለማስተላለፍ አቅዶ እና በዚህም ባቀረቡት እጩ ተወዳዳሪ መጠን 12 የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሳትፏል፡፡ ጣቢያው 18 ሠዓት የሚፈጅ የዓየር ሠዓት ለሁሉም ክርክሮች የመደበ ሲሆን እያንዳንዱ ክርክር 120 ደቂቃ የሚፈጅ እና ሰባት የተለያዩ ርዕሶች ላይ የተለያዩ ፓርቲዎች ክርክር እንዲደረግባቸው የተወሰኑ ናቸው፡፡


ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከሌሎች ተከራካሪ ፓርቲዎች በበለጠ እና በተለየ ሁኔታ ከፍተኛውን የአየር ሰዓት በመውሰድ ላዕላይነቱን ለማሳየት ሞክሯል፡፡የመጀመሪያው ክርክር የተካሄድው መጋቢት 4 እና 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት የዜና እወጃ በኋላ በሁለት ክፍሎች ተከፍሎ ሲሆን የወቅቱ የመከራከሪያ ርዕስም “የብዝሃን ፓርቲ ስርዓት እና የሰበዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በኢትዮጵያ” የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክ፣ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (አንድነት) እንዲሁም የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ለክርክሩ በአጠቃላይ ከተመደበው 120 ደቂቃ ውስጥ 45 ደቂቃዎችን ኢህአዴግ በጉዳዩ ላይ ሃሳቡን ለመግለጽ የወሰደ ሲሆን ቀሪዎቹን 75 ደቂቃዎች አራቱ ፓርቲዎች ተከፋፍለውታል፤ ይህም ለእያንድ አንዱ ፓርቲ 18 ደቂቃዎች ነው የደረሳቸው፡፡ በክርክሩ የማስተዋወቂያ ምዕራፍ ላይ የኢህአዴግ ተወካዮች ፓርቲያቸውን ለማስተዋወቅ እና በመከራከሪያ ርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ለመግለጽ 15 ደቂቃዎች የተሰጣቸው ሲሆን ሌሎቹ አራት ፓርቲዎች ለእያንድአንዳቸው ስድስት ስድስት ደቂቃዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሁለተኛው የመወያያ ምዕራፍ አራቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እያንድአንዳቸው ዘጠኝ ዘጠኝ ደቂቃዎች የደረሳቸው ሲሆን ገዢው ፓርቲ 20 ደቂቃዎች ተመድቦለታል፡፡ ገዢው ፓርቲ በሶስተኛው የማጠቃሊያ ምዕራፍ 10 ደቂቃዎች የተመደበለት ሲሆን ሌሎቹ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው አራት አራት ደቂቃዎች ነው የተሰጣቸው፡፡ በክርክር መድረኮች በተከራካሪ ፓርቲዎች መካከል እኩል ያልሆነ የሰዓት ክፍፍል ከመመደቡ በተጨማሪ ኢህአዴግ በሁለት ዋና አቅራቢዎች የተወከለ ሲሆን ሌሎቹ ፓርቲዎች እያንድአንዳቸው አንድ አንድ ዋና ተከራካሪ ነው ያቀረቡት፡፡


መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2007 ዓ.ም በብሄራዊ ቴሌቪዥን የተላለፈው ሁለተኛው ክርክር የመወያያ አጀንዳ የፌደራሊዝም ጉዳዮች ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ የክርክር መድረክ ኢህአዴግ፣አንድነት፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የመላው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክ እና የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ አልተሳተፉም፡፡ ኢህአዴግ እና አንድነት ፓርቲ በሁለተኛው የክርክር መድረክ ቀርበው ሃሳባቸውን እንዲያስረዱ ሲደረግ በመጀመሪያው የክርክር መድረክ ቀርበው የነበሩት ሶስቱ ፓርቲዎች በሁለተኛው ክርክር ላይ እንዳይቀርቡ የተደረገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ፍትሃዊ ያልሆነው የአየር ሰዓት ክፍፍል በዚህ ክርክር ላይም ቀጥሏል፡፡


የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የሆነው ኢቢሲ የገዢውን ፓርቲ እና ደጋፊዎች ብቻ ለመጥቀም ያደላ መስሎ መታየት የለበትም፡፡ መጫዎት ያለበት ሚና የሁሉንም እጩዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሸፍን መልኩ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ እና ቀጥተኛ መሆን ነው ያለበት፡፡ ከሁሉም ፓርቲዎች ምርጫን የተመለከተ የመራጮች ገለልተኛ መረጃ የማግኘት መብትን ድርጅቱ ሊያከብር የሚገባው እና ለዚህም ቅድመ-ምርመራ ቦታ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ነው፡፡


ማጠቃለያ


የግንቦት 16 ቀን ምርጫ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከፍተኛ እድገት ባስመዘገበበት ወቅት ነው፤ 10 በመቶ የሚደርስ እድገት የተመዘገበ ሲሆን ይኼውም በአፍሪካ ከፍተኛው ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ አሁንም አጠያያቂ ነው፤ በተለይ ደግሞ ሃሳብ የመግለጽ ነጻነት እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው ገደብ አሳሳቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቢቷ ኤርትራ በመቀጠል በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር በሁለተኛ ደረጃ የምትጠቀስ ሃገር ናት፡፡ የብሮድካስቲንግ እና ቴሌኮምዩኒኬሽንስ ዘርፉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው የሚገኘው፤ ያሉት ጥቂት የግል መገናኛ ብዙሃንም ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን በተደጋጋሚም ለቅድመ ምርመራ የተጋለጡ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ ያለው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ችግር በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች የመነጨ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ
• በመገናኛ ብዙሃኑ እና ሲቪክ ድርጅቶች ላይ ያለው የኢኮኖሚ አቅም ችግር
• አነስተኛ የጋዜጣ ስርጭት መጠን
• በኮምዩኒኬይሽን መሰረተ ልማቶች ላይ ተገቢ የኢንቨስትመንት ስራ አለማካሄድ ይጠቀሳሉ፡፡


እንዚህ ሁኔታዎች የግል ጋዜጠኞች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ እክል የፈጠሩ ሲሆን በተለይ በምርጫ ወቅት ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡


በዴሞክራሲያዊ አሰራር በየወቅቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች ዜጎች ለፈለጉት እጩ ድምጽ በመስጠት የፈለጉትን መንግስት መርጠው ይሰይማሉ፡፡ ይህንን ለመድረግ ስለእጩዎች እንዲሁም ፖሊሲዎቻቸው እና የኋላ ታሪካቸው ሙሉ ለሙሉ መረጃ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሃሳብ የመግለጽ ነጻነትን በተመለከተ እና በመንግስት እጅ ያለን መረጃ ጨምሮ መረጃ የማግኘት ነጻነትን የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ሚስጥራዊነት ባለ ቁጥር የመንግስትን ወሳኝ ፖሊሲዎች በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ መረጃ የማግኘት ነጻነት ህግን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያመቹ አሰራሮች ተግባር ላይ መዋል አለባቸው፣ የሃገሪቱን ሚስጥር የተመለከቱ እና ሌሎች የወንጀል ህጎች ነጻ የመረጃ ዝውውርን ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ ሊገድቡ አይገባም፡፡


አንዳቸውም ከላይ የተጠቀሱ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ የሉም፡፡ ጋዜጠኞች ሊደርስባቸው የሚችል አካላዊ ወይንም ሙያዊ ጫናን ፍራቻ የገዢውን ፓርቲ እጩዎች ደካማ ጎን የሚያንጸባርቅ መረጃ ከማሰራጨት ሊቆጠቡ እንደሚችሉ በከፍተኛ ደረጃ ጠበቃል፡፡ ጋዜጠኞቹ ለእነዚህ እጩዎች ከመጠን በላይ የሆነ ሽፋል ሊሰጧቸው እንደሚችልም በእጅጉ ይጠበቃል፡፡እንደዚህ ባለ ሁኔታ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡